በቁልቢ የሚከበረው ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል ንግሥ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
የፊታችን ሰኞ በሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል ላይ የሚገኙ ምእመናንን ደህንነት ለመጠበቅ እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።
በበዓሉ የሚታደሙ ምእመናን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን የፖሊስ መምሪያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ሓላፊ ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ፣ በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን በሚከበረው የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ንግሥ በዓል ላይ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገሮች የሚመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን እና ቱሪስቶች እንደሚታደሙ ገልጸው፣ የታዳሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና በዓሉ በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ ከሐረሪ ክልል፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከሚሊሺያ እና የመረጃ ደህንነት ሓላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የሰላም ማስከበሩን ሥራ በቅንጅት ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
በዓሉ በሚከበርበት በዞኑ ሜታ ወረዳ ሰላማ ቀበሌ ፖሊስ ዘረፋ እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ሓላፊው፣ የፀጥታ አካሉ ከወዲሁ ወደ ስፍራው መላኩን ተናግረዋል።
በተለይ በዘንድሮ በዓል የጥበቃ ሥራው ከምሥራቅ ሸዋ ሞጆ ከተማ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ጀምሮ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኢንስፔክተር ቶሎሳ፣ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ዐቃቤ ሕግ እና ጊዜያዊ ፍርድ ቤት መቋቋሙን አስታውቀዋል።
በበዓሉ ላይ እንደ ስርቆት ያሉ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ እና ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ሲያዙ የምርመራ መዝገባቸው ወዲያው ተጣርቶ አፋጣኝ የፍርድ ሂደት እና ውሳኔ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
“ምእመናን እና መንገደኞች የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ፣ ጌጣጌጦችንና ገንዘቦችን በጥንቃቄ ሊይዙ ይገባል” ያሉት ሓላፊው፣ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ምእመናን ማንኛውንም ለግጭት የሚያነሣሡ ዓርማዎችንና ምልክቶችን በክብረ በዓሉ ቦታ እና በጉዞ ላይ መያዝ እና ማንጸባረቅ እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።
ወደ ስፍራው የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ከዞኑ እና ከአጎራባች ከተሞች የትራፊክ ፖሊስ አባላት መመደቡን ጠቁመዋል።
የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ከታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከጨለንቆ ከተማ እስከ ቀርሳ ከተማ ድረስ ባለው ዋና መንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪዎች አቁሞ መሄድ እና መተላለፍ እንደማይቻል አስገንዘበዋል።
ማንኛውም ዓይነት ወንጀል ሲፈጸም እና ሲያጋጥም እንዲሁም ወድቆ የተገኘ ንብረት እና ገንዘብ ሲገኝ ምእመናን ቁልቢ ገብርኤል ገዳም ለሚገኘው ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ በስልክ ቁጥር 0253390335 ደውለው ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብር እንዲያደርጉ ሓላፊው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
Comments
Post a Comment