"ወደ ትምህርት ቤት እንመለስ" የሚል ንቅናቄ ከነገ ጀመሮ ይካሄዳል

"ወደ ትምህርት ቤት እንመለስ" የሚል ንቅናቄ ከነገ ጀመሮ ይካሄዳል።





የትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ቤት የቀሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በ በይነመረብ ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱም የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር፣የግብርና ሚኒስቴር፣ የሁሉም ክልል የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች እና የክልል ቢሮዎች ተሳትፈዋል።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ከ 9ወራት በኋላ ትምህርት ቤቶች ዳግም ወደ መማር ማስተማር ሂደት ቢገቡም ተማሪዎች የሚጠበቀውን ያህል በትምህርት ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው ተገልጿል፡፡






የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ከፊታችን አርብ ጀምሮ " ወደ ትምህርት ቤት እንመለስ" የሚል ንቅናቄ የሚጀመር መሆኑንና ሁሉም የሴክተር መስሪያ ቤቶች በንቅናቄው ላይ እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።
ንቅናቄውም ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ መሆኑንና ንቅናቄው ከትምህርት ቤት የቀሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።






በንቅናቄውም ቤት ለቤት በመዞር በየቤታቸው የቀሩ ተማሪዎች ከሰኞ ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል።
ምዝገባ ሳያደርጉ የቆዩ ተማሪዎችም እስከ ታህሳስ 23 ድረስ ምዝገባ በማድረግ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተነግሯል።
የትምህርት ሚኒስትሩ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለሰሰ በሚደረገው ጥረት በየሴክተሩ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በንቅናቄው ላይ ሁሉም የንቅናቄው አካል በመሆን በቤት የቀሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።





Comments