ጀግና የሀገር ክብር ሲነካ ይቆጣል | By Taye Dendea Aredo

ጀግና የሀገር ክብር ሲነካ ይቆጣል | By Taye Dendea Aredo






የሰሜን ምዕራብ ጎንደር ጉዳይ






በሰሜን ምዕራብ ጎንደር በኩል የኢትዮጵያ ድንበር መደፈሩን ሰምተናል። የኢትዮጵያ ጀግና በቀበሌ ጉዳይ ሳይሆን በዚህ ይንገበገባል! ጉዳዩ የሱዳን አይደለም። ከጀርባው የሁለት ሀይሎች እጅ ይታያል፡፡ አባይን እንደግል ርስቱ የሚመለከተዉ የግብፅ ጁንታ የህደሴ ግድብ ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እንዳይዉል ይፈልጋል፡፡ የእጀዙር ቀኝ ገዥዎች ደግሞ በህግ ማስከበር ዘመቻዉ ወቅት የለውጥ አመራሩ የእነሱን ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎ የአርባ ዓመት ተላላኪያቸዉን መደምሰሱን እንደድፍረት ቆጥሯል። ጀግናዉ የኢትዮጵያ መከላከያ በምስራቅ አፍሪካ ሲመለከ በነበረዉ የህወሀት ጁንታ ላይ በወሰደዉ እርምጃ ፍጥነትና ክብደት ሁለቱም ክፉኛ ደንግጧል። ኢትዮጵያን በእርዳታ አዙሪት ውስጥ በማቆየት መጫወቻ ሊያደርጓት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ " ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” ብለው ደፋ ቀና ማለት ጀምሯል፡፡





ለዓላማቸው ስኬት ደግሞ የውስጥ ባንደዎችን ተማምኗል፡፡ በርከት ያለ ባንዳ ተቆርቋሪ መስሎ በወሳኝ ሰዓት በማንነት እና በቀበሌ መሬት ስም የህዝባችንን ጠንካራ አንድነት በማላላት ብሔራዊ ጥቅሙን ለአደጋ ለማጋለጥ ይንደፋደፋል፡፡ ትክከለኛ ኢትዮጵያዊ ግን ትንሽ የቀበሌ መሬት ከአንዱ የኢትዮጵያ ክልል ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክልል ስለሄደ ማለቃቀስ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በተነካ ጊዜ ይቆጣል! በኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ይቆማል!






ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ለማንም እንደማይንበረከክ ታሪክ ይመሰክራል! አይደለም ዛሬ ላይ ያኔ እንኳን የጥቁሮችን ትክክለኛ ማንነት ለዓለም አሳይቷል! አሁን የኢትዮጵያን ክብርና ብልፅግና በአለት ላይ ለመትከል ሦስት ነገሮችን መፈፀም ግድ ይለናል፡፡ አንደኛው ዉስጣዊ አንድነታችንን ከምንጊዜዉም በላይ ማጠናከር ነዉ! ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅምን በመዘንጋት በጥቃቅን ጉዳዮች ዙሪያ መጨቃጨቅ የጠላትን አጀንዳ ማስፈፀም እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛዉ አኗኗራችንን ማስተካከል ነዉ! በተቻለ መጠን በዶላር የሚገዙ ሸቀጦችን ከመጠቀም መታቀብ ያስፈልገናል! ሀገር ወዳድ ጀግና መጠጥ ቢያምረዉ ከዉስኪ ይልቅ ጠጅን ይመርጣል።





ጀግና ዳያስፓራ ጦሙን አድሮ በህጋዊ መንገድ ለቤተሰቡ ዶላር ይልካል። ጀግና ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ ከሌብነት ፀድቶ በፍቅር እና በክብር ህዝቡን ለተጨማሪ ሰዓት ያገለግላል። ሦስት የመከላከያ አቅማችንን ማጎልበት ነዉ! እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት አርማ የሆነዉን መከላከያ ሠራዊት ቢያንስ በሞራል መደገፍ ይኖርበታል! ከውጭ እና ከውስጥ በኢትዮጵያዊ ወኔ ተሳስረን በሙሉ አቅማችን በጋራ ለጋራ ከተንቀሳቀስን ሁሉም ነገር ይቀለናል!
ባንዳ ስለቀበሌ ሲያለቃቅስ የኢትዮጵያ ጀግና ብሔራዊ ክብር በተነካ ጊዜ ይቆጣል!

Comments