የይቅርታ እና ምህረት ምንነትና በመካከላቸዉ ያለዉ ልዩነት - Federal Attorney General

የይቅርታ እና ምህረት ምንነትና በመካከላቸዉ ያለዉ ልዩነት!





የወንጀል ፍትህ ሥርዓትን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል በፖሊሲና በህግ ማዕቀፍ ውስጥ አማራጭ የመፍትሔ እርምጃ መርሆዎች መኖር እንዳለባቸው አገራት ይስማማሉ፡፡ በዚህም መሰረት ተጠርጣሪውን/ፍርደኛውን በእስር ቤት ለማቆየት የሚያስችሉ ምክንያቶች ቢኖሩም መንግስት ጥፋተኛው ማረሚያ ቤት ከሚቆይ ይልቅ ሕብረተሰቡን ቢቀላቀል የተሻለ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያበረክታል ብሎ በሚያስብበት ጊዜ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት እነዚህን ሁኔታዎች ለማረጋጋትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ለማምጣት ከእስር ውጪ ያሉ አማራጮችን ተግባራዊ የማድረግ አቅጣጫን ይከተላል፡፡
ይቅርታ እና ምህረትም በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ በስፋት የሚታወቁ ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ገለፃ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የይቅርታ ቦርድ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ዘለቃ ዳሎል በሰጡን ማብራሪያ ላይ ተንተርሰን ስለ ይቅርታና ምህረት ምንነታቸው እና ልዩነታቸውን እንመለከታለን፡፡መልካም ንባብ!
ሀ)ይቅርታና ምህረት ምንነት፡-






ይቅርታ






ይቅርታ በአገራት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ በስፋት የሚታወቅና የበኩሉ ወሳኝ ጠቀሜታ ያለው ከወንጀል ሕግ ዓላማ መተግበሪያ ስልቶች ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡ ትርጓሜዉንም አንድ ሰው ከፈፀመው ወንጀል ወይም ከተፈረደበት የወንጀል ጥፋተኝነትና ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ነፃ የሚሆንበት መንግሥታዊ ውሣኔ እንደሆነ በተለያዩ ጽሁፎች ውስጥ እናገኛለን፡፡ የኦክስፎርድ አድቨንስድ ለርነር ዲክሽነሪ ይቅርታን “an official decision not to punish somebody for a crime” በማለት ይገልፀዋል፡፡ ግርድፍ የአማርኛ ትርጉሙም “ይቅርታ አንድን ግለሰብ ከወንጀል ቅጣት ነፃ የሚያደርግ የመንግስት ውሰኔ ነው” እንደ ማለት ነው፡፡ የመንግስት ዉሳኔ ሲባል በተለይ የህግ አስፈጻሚ አካል ዉሳኔ መሆኑን ከነባራዊው የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሁኔታዎች መረደት ይቻላል፡፡
በዚህም እሳቤ በአገራችን የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ-ሥርዓትን ለመምራት በወጣው አዋጅ ቁጥር 840/2006 ይቅርታ “የቅጣት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣት ፍርዱ አፈፃፀምና ዓይነት ቀለል ተደርጐ እንዲፈፀም ማድረግ ነው” በሚል ተተርጉሟል፡፡ የቅጣት ፍርድ ማለት ደግሞ በወንጀል ጉዳይ ዋና ቅጣትን፣ ተጨማሪ ቅጣትን ወይም የክልከላና የጥንቃቄ እርምጃን በተመለከተ በፍርድ ቤት የተሰጠ የመጨራሻ ውሳኔ እንደሆነ አዋጁ ይገልፃል፡፡






ምህረት






ምህረት በበርካታ የዓለም አገራት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ የሚያገለግል ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በተለያዩ ፀሀፍቶች ከተሰጠው ትርጉም በመነሳት ምህረት ሕገ መንግስታዊ አግባብ ያለው ሆኖ ከፍተኛ ሥልጣን ባለው የመንግስት አካል በአብዛኛው ለፖለቲካ ወንጀል ፈፃሚዎች (ለምሳሌ፡- በሕገ መንግሰትና በሕገመንግታዊ ስርዓት ላይ ለተፈፀሙ ወንጀሎች፣ የሀገር መክደት፣ የአመፅ ወንጀሎችን እና በሀገርና በመንግስት ላይ አመፅ ማነሣሣትና መሰል ድርጊቶችን ለፈፀሙና በሕግ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰው የመንግስትን ሕግ እና ሥርዓት ለማክበር ግዴታ ለሚገቡ ወይም ሊገቡ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡ ጥቂት ወይም ለሁሉም ወንጀለኞች መንግስት ያለፈውን ጥፋታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሰርይበት (እንዳልተሰራ የሚቆጥርበት) አግባብ ነው፡፡
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የታወጀው የምህረት አሰጣጠና አፈፃፀም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1089/2010 “ምህረት” ማለት የወንጀል ምርመራ ከመጀመሩ በፊት፣ ከተጀመረ በኋላ፣ የክስ ሂደት ላይ እያለ ወይም የወንጀል ቅጣት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የቅጣት ውሳኔ ያገኙ ሰዎችን ያለምንም ገደብ ወይም በአንዳንድ ገደቦች ወይም ግዴታዎች ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ነው በማለት ተርጉሞታል፡፡






ለ) የይቅርታና ምህረት ልዩነት፡-
ይቅርታ በወንጀል ጉዳይ በፍርድ ቤት የመጨራሻ ውሣኔ የተወሰነ ዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት ወይም፣ የጥንቃቄና ጥበቃ እርምጃ/ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ነፃ ለማድረግ በይቅርታ ቦርድ አማካኝነት በሚቀርብ የውሣኔ ሃሣብ መነሻ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 71/1 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት በኘሬዝዳንት የሚወሰን ውሳኔ ሲሆን በክርክር ላይ ያሉ ጉዳዮች ለይቅርታ የሚቀርቡበት አግባብ የለም፡፡ በሌላ በኩል በአዋጅ ቁጥር 840/2006 መሰረት ይቅርታ በግል መጠየቅ የሚቻል ሲሆን (ታራሚው፣ ጠበቃው ወይም ወኪሉ አንቀፅ 15/2/) ይቅርታ ለመጠየቅ የፈለገበትን ምክንያትና የተለያዩ ደጋፊ ማስረጃዎችን የማቅረብ ግዴታም ይኖርበታል፡፡ በአንቀጽ 15/2 መሰረት በመንግስት የሚጠየቅ ይቅርታ ሆነ በታራሚው ቤተሰቦች፣ ጠበቃ ወይም ወኪል የሚጠየቅ ይቅርታ ዋጋ የሚኖረው ታራሚው ሲስማማ/ሲፈርም ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀጽ 15 (3) በስሙ የይቅርታ ጥያቄ የቀረበለት ታራሚ በይቅርታ ጥያቄው የሚስማማ መሆኑን በመግለጽ በይቅርታ ማመልከቻ ላይ መፈረም አለበት በማለት ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም ይቅርታ ለግለሰብ የሚሰጥ ሲሆን አንድ ሰው ይቅርታ ለመጠየቅ በተከሰሰበት ወንጀል የተፈረደበትና ማረሚያ ቤት የሚገኝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይቅርታ በቅድመ ሁኔታና ያለቅድመ ሁኔታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ይቅርታ የሚሰጠው ታራሚው በፈፀመው ወንጀል የተፀፀተ፣ የታረመ እና አምራች ዜጋ ለመሆን ዝግጁ የሆነ መሆኑን በማረጋገጥ ነው፡፡






ይቅርታ በሙሉ (ከእስር መፍታት) ወይም በከፊል (የእስራት ቅጣት መቀነስ) የሚሰጥ እና የወንጀል ሪከርድን የማይሰርዝ ከመሆኑም በተጨማሪ በቅድመ ሁኔታ ወይም በተሳሳተ መረጃ የተሰጠ ይቅርታ ተሰርዞ ታራሚው የተፈረደበትን ቅጣት ተመልሶ እንዲፈጽም የሚደረግ ሲሆን ከወንጀል ውሳኔው የሚመነጩ የፍትሀብሄር ኃላፍነቶችንም የሚያስቀር አይሆንም፡፡






ይህ በእንዲህ እንዳለ ምህረትን በተመለከተ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 230 ላይ ምህረት ለአንድ አይነት ወንጀሎች ወይም በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ወንጀለኞች ያለምንም ገደብ ወይም በአንዳንድ ገደቦች ወይም ግዴታዎች የሚሰጥ መሆኑን፣ የአሰጣጡም ሁኔታ በህግ እንደተደነገገው ሆኖ ህጉ ዓላማውን፣ የተጠቃሚዎቹን ማንነትና የተፈፃሚነት ወሰን በግልፅ መወሰን እንዳለበት ደንግጓል፡፡
በተጨማሪም ምህረት ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ማናቸውም የወንጀል ክስ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል ያግዳል፣ ምህረት በሚሰጥበት ጉዳይ ቅጣት ተወስኖ እንደሆነ ምህረቱ ቅጣቱንና ቅጣቱ የሚያስከትለውን ማናቸውንም ሌሎች የወንጀል ውጤቶች እንደሚያስቀር እና የጥፋተኝት ውሳኔም እንዳልነበረ ተቆጥሮ ከወንጀለኞቹ መዝገብ ላይ እንደሚሰረዝ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ምህረት ከይቅርታ በተለየ መልኩ ለግለሰብ ጠያቂ ሳይሆን ለቡድኖች ወይም ለተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶች በተወሰነ የጊዜ ገደብ የሚሰጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይቅርታ የወንጀል ሪከርድን የማይሰርዝ ሲሆን ምህረት ግን ወንጀሉ እንዳልተፈፀመ ቆጥሮ የወንጀል መዝገብን ይሰርዛል፡፡ ምህረት ሲሰጥ ቅድመ ሁኔታ የማይኖረውና ከተሰጣም በኋላ የማይሰረዝ ነው፡፡






ከዚህ በተጨማሪ ምህረት ለመስጠት እንደ ይቅርታ ወንጀለኛው የመጨራሻ ፍርድ ያገኘ እና በማረሚያ ቤት የታሰረ ብቻ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ይልቁኑም ምህረት በተደረጉ ወንጀሎች የተጠረጠረ፣የተከሰሰ፣የተፈረደበትና ማረሚያ ቤት የገባ ወንጀለኛ በሙሉ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በታወጀው የምህረት አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1089/2010 መሰረት ምህረት የሚሰጠው ምህረት ለመስጠት የተፈለጉ የወንጀል ዓይነቶች ወይም ወንጀለኞች ከተለዩ በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን በተመለከተ አዋጅ ሲወጣ ብቻ ነው፡፡






ይቅርታም ሆነ ምህረት በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 28 ለተዘረዘሩ ወንጀሎች አይሰጥም፡፡ እነዚህም የሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር ወይም ኢ- ሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶችን መፈፀም ናቸው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ወንጀሎች መነሻ የሞት ፍርድ ተፈርዶ ከሆነ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሞት ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት መቀየር እንደሚችሉ ህገ መንግስቱ ደንግጓል፡፡

Comments