በኢትዮጵያ በቅርቡ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ አገራዊ የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ ተገለፀ።
"ማይንድ ኢትዮጵያ" ሁሉን አቀፍና አሳታፊ አገራዊ የምክክር መድረክ እንደሚያዘጋጅ አስታወቀ።
ውይይቱም በዋናነት በድህረ ምርጫ ጊዜያት ውስጥ ባሉ አንኳር የአገር ግንባታና ሌሎች ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።
"ማይንድ ኢትዮጵያ" የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ "ደስትኒ ኢትዮጵያ" እና ሌሎች ስምንት ባለድርሻ አካላትን የያዘ አገር አቀፍ ጥምረት ነው።
ጥምረቱ በተለይ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ትብብር እንዲፈጠር የሚሰራ ሲሆን፤ በቅርቡም የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ እለት ቀደም ብሎ በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች የመልካም ምኞት መግለጫ መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።
የ"ደስትኒ ኢትዮጵያ" መስራችና የ"ማይንድ ኢትዮጵያ" አባል ዶክተር ንጉሱ አክሊሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጥምረቱ በቅርቡ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል።
አሁን ላይ "አጀንዳዎቹ ምን ይሁኑ? እነማን ይሳተፉ? እንዲሁም አወያዮቹ እነማን ይሁኑ?" በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳብ የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በመድረኩ አንድ ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዶክተር ንጉሱ፤ ማይንድ ኢትዮጵያ መድረኩን ከማመቻቸት ያለፈ ሚና እንደማይኖረው ተናግረዋል።
ውይይቱ የመንግስትም ሆነ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት እንደሌለውና አገር በቀል እሴቱን ጠብቆ እንደሚከናወንም አንስተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፤ የአርብቶ አደሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን ጨምሮ 22 ባለድሻ አካላት በመድረኩ እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ባለድርሻ አካላት ተብለው ከተለዩ አካላት ጋር በመገናኘት የውይይት አጀንዳዎችን የመሰብሰብ፣ ተወካይ የመቀበልና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች እንዲሁም በጥቆማ የሚመጡ የህብረተሰብ ተወካይ እና አወያዮች ስም ራሱን በቻለ ቋት እየተሰበሰበ መሆኑንም ዶክተር ንጉሱ ጨምረው ተናግረዋል።
በቋት የተሰበሰበውን አጀንዳ የመምረጥና ቅደም ተከተል የመወሰኑ ስራ ለወይይቱ በሚመረጡ ሰዎች እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ጊዜያት ሁሉንም ክልሎች፣ የፖለቲካ አመለካከቶችና ሌሎች ልዩነቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ተሳተፊዎችን የመለየት ስራ እንደሚጀመርም አንስተዋል።
"ደስትኒ ኢትዮጵያ" ከዚህ ቀደም 50 የሚሆኑ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመያዝ ባደረገው ምክክር ላይ "ሰባራ ወንበር"፤ "የፉክክር ቤት"፤ "አፄ በጉልበቱ" እና "ንጋት" በሚሉ የቢሆን እይታዎች ማስቀመጡን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም በያገባኛል መንፈስ ከሰራ የአገሪቷ መጻኢ እድል ብሩህ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በተለይ በተቋማት ግንባታ፣ አገራዊ እርቅ፣ አገራዊ ምክክር ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራ ኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ "ንጋት" መሆኑን አንስተዋል።
Comments
Post a Comment